የ’አዲስ መሶብ’ ዲጂታል የአንድ ማዕከላት የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግ ብልሹ አሰራርን አስቀርተዋል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የ’አዲስ መሶብ’ ዲጂታል የአንድ ማዕከላት የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግ ብልሹ አሰራርን አስቀርተዋል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2018(ኢዜአ)፦የ'አዲስ መሶብ' የአንድ ዲጂታል ማዕከላት የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግ ብልሹ አሰራርና ሙስናን ማስቀረታቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ 4ኛውን የ'አዲስ መሶብ' ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ የ'አዲስ መሶብ' የአንድ ማዕከላት አገልግሎት የተገልጋዮችን እንግልት በማስቀረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሰጡ 240 የአገልግሎት አይነቶችም በዲጂታል ሥርዓት እየተሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የተለያዩ የአገልግሎት አይነቶችንም በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማስገባት ተገልጋዮች ያለአንዳች እንግልት የሚገለገሉበትን ምቹ ምኅዳር መፍጠር እንደተቻላ አንስተዋል።
የ'አዲስ መሶብ' ዲጂታል የአንድ ማዕከላትም የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ በማሳደግ ብልሹ አሰራርና ሙስናን ማስቀረት ማስቻሉን አስረድተዋል።
በቀጣይም ዜጎች በያሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበትን ተንቀሳቃሽ የ'አዲስ መሶብ' ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ በሁሉም መስክ በለውጥ ምህዋር ውስጥ ናት ብለዋል።
በዚህም የ'አዲስ መሶብ' የአንድ ማዕከላት አስተማማኝ የኃይልና የኔትወርክ አቅርቦት እንዲኖራቸው በማድረግ የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት በጥራት እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር)፤ በክፍለ ከተማው ተገንብቶ የተመረቀው የ'አዲስ መሶብ' ዲጂታል የአንድ ማዕከል ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ ማዕከል ነው ብለዋል።