ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት - ኢዜአ አማርኛ
ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት
በሙሴ መለሰ
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ያቀረበችው እ.አ.አ 2003 ነበር።
ኢትዮጵያ በወቅቱ ጥያቄውን ካቀረበች በኋላ የታዛቢነት (Observer) ደረጃን አገኝታለች።
እ.ኤ.አ በ2006 የውጭ ንግድ ፖሊሲዋን የሚገልጽ ሰነድ ለድርጅቱ አቅርባለች።
ሰነዱ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች፣ የወጪና ገቢ ንግድ ሕጎች፣ የቀረጥ፣ ከቀረጥ ውጭ ያሉ የንግድ ገደቦች፣ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ እና የኢንቨስትመንት ሕጎችን ያካተተ ነበር።
በኢትዮጵያ እና በዓለም ንግድ ድርጅት መካከል የመጀመሪያው የድርድር ምዕራፍ የተጀመረው እ.አ.አ በ2008 ነው።
ከእ.አ.አ 2008 እስከ 2012 በቆየው የቴክኒክ ድርድር ሶስት የስራ ቡድን ስብስባዎች ተካሂደዋል።
በዚህ ወቅት የነበረው ድርድር በዋናነት ኢትዮጵያ ስለ ንግድ ሥርዓቷ ማብራሪያ የምትሰጥባቸው እንጂ፣ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘት አልቻሉም።
ከእ.አ.አ 2012 እስከ 2019 የሁለቱ ወገኖች ድርድር ተቋርጦ ነበር፤ ለሰባት ዓመታት እንዲቋረጥ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ።
በወቅቱ ስልጣን የነበረው የኢህአዴግ መንግስት "የገበያ ውድቀት" አለ ብሎ ያምን ነበር። ስለዚህም እንደ ባንክ፣ ቴሌኮም እና ኢነርጂ ያሉ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች በመንግስት እጅ መቆየት አለባቸው የሚል አቋም ነበረው።
ይህ የመንግስት ጽንሰ ሀሳብ ድርጅቱ የተለያዩ ዘርፎች ለውጭ ክፍት መደረግ አለባቸው ከሚለው አቋም ጋር የሚጣጣም አልነበረም።
በዓለም ንግድ ድርጅት የተጠየቁ የንግድ ስርዓትን የማዘመን ስራዎች በሚፈለገው መልኩ አለመሄዳቸውም ለድርድሩ መቆም እንደ ምክንያትነት ይነሳል።
የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ የአባልነት ድርድር በድጋሚ ነፍስ ዘርቷል።
መንግስት በተለያዩ ዘርፎች የወሰዳቸው ጠንካራ የንግድ እና ኢኮኖሚ እርምጃዎች ድርድሩ በአዎንታዊ መልኩ እንዲቀጥል አድርጓታል።
መንግስት እንደ ቴሌኮም፣ ባንክ እና ሎጅቲክስ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉ በድርጅቱ እንደ ትልቅ ለውጥ የታየ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያን ሕጎች ከድርጅቱ ህጎች ጋር የማጣጣም ስራም ተከናውኗል።
ከ60 ዓመታት በላይ ያገለገለው የንግድ ሕግ ማሻሻያ ተደርጎበት ዘመናዊ የንግድ አይነቶች የተካተቱ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ መቋቋም የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ኢትዮጵያ የሸቀጦች ታሪፍ ቅናሽ ሰነዷን አሻሽላ አቅርባለች። ይህም ኢትዮጵያ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የምትጥለው ቀረጥ በምን ያህል መጠንና በስንት ዓመት ውስጥ እንደሚቀንስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገባችውን ቃል በተግባር ያሳየችበት ነው።
በአሁኑ ሰዓት በዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በተናጠል እንደ ቻይና፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ካናዳ ካሉ ሀገራት እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር የገበያ ተደራሽነት ድርድር እያደረገች ነው።
በተደረጉት የተናጥል ድርድሮች ላይም ለኢትዮጵያ አባልነት ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ከአዕምሯዊ ንብረት ጋር በተያያዘ የፈጠራ ውጤቶችን፣ የንግድ ምልክቶችን እና የባህል እሴቶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ሕግና ተቋም መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጓል።
የጉምሩክ አሰራር የሸቀጦችን ፍሰት ለማሳለጥ የዲጂታል ጉምሩክ አሰራርን የማስፋፋት ስራ በመንግስት በኩል ተከናውኗል።
14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብስባ ከመጋቢት 17 እስከ 20 ቀን 2018 ዓ.ም በካሜሮን ያውንዴ መካሄድ ጀምሯል።
በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክም በስብስባው ላይ ለመሳተፍ ያውንዴ ገብቷል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከስብስባው ጎን ለጎን የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን ሚኒስትሩ ከዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ (ዶ/ር) ጋር ያደረጉት ውይይትም በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
በውይይቱ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የጀመረችው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለድርጅቱ አባል አገራት ከ1200 በላይ ለሚሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቷንና ከ419 በላይ የሕግና የፖሊሲ ይዘቶችን ማሳወቋን ጠቁመዋል።
የያውንዴው ስብስባ ለኢትዮጵያ የአባልነት ጉዞ የፖለቲካ ድጋፍን ለማሰባሰብ ያስችላታል።
በቅርቡ የድርጅቱ አባል ከሆኑ የአፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት ጋር የቴክኒክ እና የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግም ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርላታል።
የያውንዴው ውይይት ኢትዮጵያ በቴክኒክ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ደረጃም ለድርድር ዝግጁ መሆኗን የምታሳይበት ነው።
የዓለም የንግድ ድርጅት እ.አ.አ በ1995 የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫው ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ነው።ድርጅቱ 166 አባል ሀገራት አሉት። አባል ሀገራቱ የዓለምን 98 በመቶ የንግድ ልውውጥን እንደሚሸፍኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓለም ንግድ ድርጅት በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አቅምና ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው። ድርጅቱ ራሱ ገንዘብ የሚያበድር ባንክ ባይሆንም፣ የዓለምን የንግድ “የጨዋታ ሕግ" በመቅረጽ ረገድ ያለው ሚና ትልቅ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆኗ የገበያ እድሏ እንዲሰፋ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ምርቶች በ160+ አባል አገራት ገበያ ውስጥ ያለ አድሎና በዝቅተኛ ታሪፍ እንዲገቡ ዕድል ይሰጣል።
ይህ በተለይም ለግብርና ውጤቶችና ለጨርቃጨርቅ ምርቶች ትልቅ በር ይከፍታል።
የኢትዮጵያ አባል መሆን ሀገሪቷ ዓለም አቀፍ የንግድ ሕጎችን እንደምታከብር ማረጋገጫ ስለሚሆን፤ ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር ያደርጋል።
ኢትዮጵያ አባል መሆኗ ከሌሎች አገራት ጋር የንግድ አለመግባባቶች ቢገጥሟት፣ በድርጅቱ የክርክር መፍቻ መድረክ አማካኝነት መብቷን ማስከበር ትችላለች።
ኢትዮጵያ የንግድ አቅሟን ለመገንባት የሚያግዙ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችንና የቴክኒክ ድጋፎችን ከድርጅቱ ማግኘት ትችላለች።
ኢትዮጵያ በያዘችው ፍጥነት እና ቁርጠኝነት ከቀጠለች እ.አ.አ 2026 የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድሯን የማጠናቀቅ እድሏ ሰፊ ነው።
የድርድሩ መጠናቀቅ ስምምነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቅ እና የአገር ውስጥ ህጎችን ከድርጅቱ ሕግ ጋር የማጣጣም ስራዎችን ጨምሮ በቀጣይ ምዕራፍ ለሚከናወኑ ስራዎች በር ይከፍታል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን ውጥኗ ከ23 ዓመታት በኋላ እውን ሊሆን የተቃረበ ሲሆን ድርድሩም ወደ መደምደሚያው ምዕራፍ ደርሷል።