በክልሉ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ተቀናጅቶ በመስራቱ ለሕዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማድረስ እየተቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ተቀናጅቶ በመስራቱ ለሕዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማድረስ እየተቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ተቀናጅቶ በመስራቱ ለሕዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማድረስ እየተቻለ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ፎረም የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና በቢሮው የተዘጋጀው የተቀናጀ ድረ ገጽ ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ቢሮው የክልሉን መረጃ በበላይነት የማስተዳደር እና መልካም ገጽታን የመገንባት ስራ በትኩረት እያከናወነ ነው።
ቢሮው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲኖር የማድረግ እንዲሁም የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን የማስተባበር ተግባር እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ተቀናጅተው መስራት እንዲችሉ የጋራ ፎረም በመቋቋሙ የጋራ ትርክት ግንባታውን ለማጠናከርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው መረጃን አቀናጅቶ የሚይዘው ድረ-ገጽም ዘመናዊ የመረጃ አስተዳደርን፣ በእውነተኛ መረጃ ላይ የተገነባና ተደራሽነቱ አስተማማኝ የሆነ አሠራርን እውን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ ዘመን ሊያጋጥሙ የሚችሉ የመረጃ አገልግሎት ፈተናዎችን ለመከላከል ቢሮው የመረጃ አስተዳደር ማዕከል በመገንባት አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ድረ ገጹ በየደረጃው ከሚገኙ የኮሙኒኬሽን መዋቅሮች መረጃ ከመሰብሰብ ባለፈ በሚዲያ፣ በመንግሥት ተቋማትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑንም አስረድተዋል።
ድረ ገጹ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግብ አካል መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ቢሮው በሁሉም ረገድ አገልግሎቱን ወደ ዲጂታል በመቀየር፣ ጥራት ያለውና ወጥ የሆነ መረጃን ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ፎረሙ በዘርፉ የተናበበ እና የተቀናጀ አሰራር እንዲኖር እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ይፋ የተደረገው ድረ-ገጽም በክልሉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ተደራሽ በማድረግ የሕዝቡን የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
በመድረኩም የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የጀመረው የዲጂታል መረጃ አስተዳደር ሥርዓት እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና ቀርቧል።