የጅማ ከተማ ነዋሪዎች በምርጫው በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ እየወሰዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ከተማ ነዋሪዎች በምርጫው በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ እየወሰዱ ነው
ጅማ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ መሆናቸውን የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ለዚሁ ተግባር የምርጫ ካርዳቸውን ሲወስዱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ነዋሪዎች እንዳሉት በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለሀገራቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸው እየተወጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌታቸው ወዳጆ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ካርዳቸውን ከመውሰዳቸው ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጫቸውን በመገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡበትን መድረክ እየተከታተሉ መሆኑን አንስተዋል።
ሌሎችም እንደሳቸው በወቅቱ የምርጫ ካርዳቸውን በመውስድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ለሀገሪቱ እድገት የሚበጅ ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ እንዲመርጡም መክረዋል።
የምርጫ ካርድ መውሰድ ለሀገር እድገት የሚበጅ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ መሰረት በመሆኑ ካርድ መውሰዱን የገለጸው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ዘሪሁን ጂሀድ ነው።
በምርጫ ካርዱም የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እና የሀገሪቱን እድገት የሚያስቀጥል ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ሌላኛዋ የጅማ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አለምፀሀይ ፃዲቁ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የሚያስችል የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረው ለህዝብ እና ለሀገር እንዲሁም ለሴቶች ተጠቃሚነት በትኩረት ይሰራል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ እንዳቀዱም አክለዋል።