ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስኬት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባራዊ ውጤት ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ንግድና ኢንቨስትመንት ስኬት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባራዊ ውጤት ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ገለጹ።

በ4ኛ 'ኢንቨስት በኢትዮጵያ' ፎረም ''ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ዝግጁ ናት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፤ ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነትን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

4ኛው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፎረምም የቢዝነስ ለቢዝነስ ትብብርን በማጎልበት የጋራ መግባባትና ትብብርን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ የንግድና ኢንቨስትመንት ስኬት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባራዊ ውጤት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በወሳኝ የዕድገት ምዕራፍ ላይ እየተጓዘ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም ለንግድና ኢንቨስትመንት አስቻይ ሥነ-ምኅዳር መፈጠሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ታዳሽ ኃይል፣ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መክፈት ማስቻሉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከልነትን የሚያረጋግጥ የዕድገት ውጤት እያስገኘ መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይም ዓለም አቀፍ አልሚ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ የፈጠረቻቸውን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም