መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ተግባራዊ ያደረጋቸው ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ተግባራዊ ያደረጋቸው ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ተግባራዊ ያደረጋቸው ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በ4ኛ 'ኢንቨስት በኢትዮጵያ' ፎረም ''ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ዝግጁ ናት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ዝግጁነት በተግባር እያረጋገጠች መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በኢንቨስትመንት መስክ እውነተኛ ሽግግር ላይ ትገኛለች።
የዘንድሮው ፎረም መሪ ሃሳብም የፍላጎት መግለጫ ሳይሆን፣ በተግባር የታየ እድገትን፣ ግልጽ አሰራርንና ቀልጣፋ አገልግሎትን የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ትልቁ ለውጥ የታየው አቅምን ከማስተዋወቅ ባለፈ ውጤትን ወደ ማሳየት፣ ከውይይት ደግሞ ወደ ተግባር መሸጋገራችን ነው ብለዋል።
ለዚህም እንደ ማሳያ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን "በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ" ፎረምን ከ58 ሀገራት የተወጡ ከ750 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመት የኢንቨስትመንት ቃል ኪዳን መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲነቃቃና ተመራጭነቱ እንዲጨምር ያከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አማካኝነት በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በህግ ማዕቀፎችና በተቋማዊ አሰራሮች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ለዘርፉ መጠናከር ትልቅ መሰረት መጣላቸውን ተናግረዋል፡፡
ወደ ትግበራ የገቡ በርካታ ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶችን ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር አቅሟን እያጠናከረች መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሪፎርሙ የታሰበውን ግብ እንዲመታና የሀገሪቱ ብልፅግና እንዲረጋገጥ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርባቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።