ቀጥታ፡

የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ በውጭ ገበያ ተፈላጊነቱን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

አዳማ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ በውጭ ገበያ ተፈላጊነቱን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለጸ።

የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነት የሚያረጋግጡ ደንቦችን እንዲሁም የጥራት ማስጠበቂያ ስታንዳርዶች ተዘጋጅተው እየተሰራ ይገኛል።

ከእንስሳት ጤና አጠባበቅና አያያዝ ጀምሮ የምርት ጥራትን በተለያዩ ስታንዳርዶችን በማስጠበቅ ለገበያ ማቅረብና ተፈላጊነቱን የማሳደግ ተግባር ትኩረት ተደርጎበት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አያሌው ሹመት፤ ሀገሪቷ ካላት ሰፊ የእንስሳት ሃብት አንፃር ተጠቃሚ እንድትሆን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የስጋ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ያሉ ባለሃብቶች ጋር በቅርበት በመስራት የምርት ጥራትና ደህንነትን በማስጠበቅ ተፈላጊነቱን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ ስራን ጨምሮ የዘርፉን ሙያተኞች አቅምና ክህሎት የማሳደግ እንዲሁም የቄራዎች የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከቄራዎች የሚወጣው ደረቅ ቆሻሻ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ እየዋለ መሆኑን ጠቁመው፤ ፍሳሽ ቆሻሻም ታክሞ ለአገልግሎት እንዲውል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የዘመናዊ የኳራንቲን ግንባታ በማካሄድ የተሳካ ውጤት ማምጣት መቻሉንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የእንስሳት ሀብት ልማት ስትራቴጂ በመቅረጽ ምርቱን በዘመናዊ አሰራር እሴት ተጨምሮበት ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህም መሰረት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ ለውጭ ገበያ ተፈላጊነቱን ለማሳደግ የሚደረገው የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም