በሶማሌ ክልል ወጣቶች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ወጣቶች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ
ጅግጅጋ፣ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ወጣቶች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ከማድረግ ባሻገር ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት ገለጸ።
በጠቅላላ ምርጫው ለመሳተፍ ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች አንዱ የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ዋነኛው በመሆኑ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በሚባል ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠቅላላ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲከናወን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
የሶማሌ ክልል ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሀመድ አህመድ ኑረ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የክልሉ ህዝብ በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የምርጫ ካርዱን በወቅቱ እንዲወስድ እየተሰራ ነው።
የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤትም የወጣቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግና በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶች ህገ መንግሥታዊ የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዜጎች በምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰድ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በተጓዳኝም ወጣቶቹ ቀደም ብለው ሲሳተፉበት የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማጠናከር በደም ልገሳ፣ አረጋውያንን በመርዳት እንዲሁም በሌሎች ተግባራት ላይ እየተሣተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወጣቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዲጂታል ክህሎታቸውን የማበልጸግ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ የተጀመሩ ተግባራትም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም ወጣቶቹ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ላይ እንዲሳተፉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።