ቀጥታ፡

በሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መጀመሩ ከእንግልትንና ከተጨማሪ ወጪ ታድጎናል

ወራቤ ፤ መጋቢት 17/2018(ኢዜአ) ፡-በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መጀመሩ አገልግሎቱን ለማግኘት ይደርስብን የነበረውን እንግልትና ተጨማሪ ወጪን ያስቀረ ነው ሲሉ ተገልጋዮች ገለፁ፡፡

የወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ማዕከል  ወደ አገልግሎት መግባት ህክምናውን በቅርበት እንዲከታተሉ እንዳገዛቸው ለኢዜአ  አስተያየታቸውን የሰጡ  ተገልጋዮች ገልጸዋል።

ከተገልጋዮች መካከል የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት  አቶ ዮሀንስ ሳህሌ  ፤ ላለፉት ሰባት ዓመታት የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማግኘት ወደ  አዲስ አበባ መጓዝ የግድ ነበር ይላሉ፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ ከህመማቸው   ቶሎ ለማገገምም ይቸገሩ እንደነበር ነው የሚያስታውሱት።

በአሁኑ ወቅት ግን  የህክምና አገልግሎቱ በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል መሰጠቱ ጤናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ እንግልትና ተጨማሪ ወጪን ያስቀረ ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ታደለች ላሞሬ በግል የህክምና ተቋም የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማግኝት   የሚጠየቀው ገንዘብ ለከፍተኛ ወጪ ዳርጓቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

የወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ማዕከል  አገልግሎት መጀመሩ ህክምናቸውን በአግባቡ ለመከታተል  እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

የሆስፒታሉ  የኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎት ቀልጣፋና ለተገልጋዮች ምቹ ከመሆኑም በተጨማሪ በህክምና ባለሙያዎችም የሚደረግላቸው ክትትል ጤናቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ማድረጉን ነው የሚናገሩት፡፡

በስልጤ ዞን በቅበት ከተማ ነዋሪው አቶ መሀመድ ኢሳ በበኩላቸው፤  የኩላሊት  ሕክምና ለማግኝት   በአዲስ አበባ ከተማ  ቤት ተከራይተው  ይቀመጡ እንደነበር ይናገራሉ።

በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የተጀመረው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ሲደርስባቸው የነበረን እንግልትና ወጪን ያስቀረላቸው ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡

በሆስፒታሉ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰቡን እንግልት ለማስቀረት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ የተናገሩት ደግሞ በሆስፒታሉ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ ቢላል ናቸው፡፡

ሆስፒታሉ በመደበኛነት ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎቶች በተጨማሪ ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ሪፈር የሚደረጉ ታማሚዎችን ለማስቀረት  ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም የኩላሊት እጥበት ፣ የዳሌ ንቅለ ተከላ ፤የፎረንሲክ ህክምና አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶች ስለመጀመሩ ለአብነት  ጠቅሰዋል።

በአቅራቢው የህክምና  አገልግሎቱን ለማግኘት ማህበረሰቡ ይደርስበት የነበረውን የጉዞ  ወጪና እንግልት ለመቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም