ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ዝግጁ የሆነች፣ የዕምቅ ዐቅሞችና ዕድሎች መሶብ ናት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ዝግጁ የሆነች፣ የዕምቅ ዐቅሞችና የዕድሎች መሶብ ናት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ አራተኛውን "Invest in Ethiopia 2026" የቢዝነስ ፎረምን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ዝግጁ የሆነች፣ የዕምቅ ዐቅሞችና የዕድሎች መሶብ ናት ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት።


 

ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ብቻ አይደለችም፤ ዛሬ በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ያለች፣ ግዙፍና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እየገነባች የምትገኝ ሰፊና አዋጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት ብለዋል።

የኢንቨስትመንት መሶባችን በትጉኅና ወጣት ሕዝብ ዐቅም፣ ባልተነካ የተፈጥሮ ጸጋ እና በስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የታደለ መሆኑን አመልክተዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርማችንና በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያችን ለዘመናዊና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የማይመቹ አሠራሮችን በቆራጥነት በመቀየር እንደ ፋይናንስና ቴሌኮም ያሉ ቁልፍ ዘርፎችን ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጋቸውን ነው ያወሱት።

የመሠረተ ልማት አውታር መስፋፋቱ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ መፈጠሩ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ምኅዳርና ቁርጠኝነት ለዓለም የሚያረጋግጡ ታላላቅ ማሳያዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

እኛ የምንፈልገው ድጋፍ ሳይሆን አጋርነትን ነው፤ ርዳታን ሳይሆን ኢንቨስትመንትን ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ለባለ ሀብቶች ምቹ፣ ግልጽና ተራማጅ የሆነ የሕግ ማሕቀፍ አዘጋጅተናልም ብለዋል።

መንግስት የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው በግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ፣ በፈጠራና በርትዕ በሚመራ የኢኮኖሚ ምኅዳር መሆኑን በጽኑ እንደሚያምን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ካፒታል፣ ለችሎታ እና ለዕድል በሯን ወለል አድርጋ መክፈቷንም አመልክተዋል።

የዛሬው መድረክም ራዕይን ከተግባር፣ ዕቅድና መሻትን ደግሞ ከኢንቨስትመንት ጋር በማገናኘት የጋራ ብልጽግናችንን የምንቀርጽበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን በፍጥነት ወደ ከፍታ እየገሠገሠች ባለችበት በዚህ ታሪካዊ የዕድገት ጉዞ፣ ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች ኢትዮጵያ ለእናንተ ዝግጁ የሆነ፣ በዕድሎችና በስኬቶች የተሞላ ታላቅ የኢንቨስትመንት መሶብ አላት፤ ኑ አብረን እንሥራ! ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም