ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያን የቀጣናው ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስተመንት ፍሰትን በማሳደግ ኢትዮጵያን የቀጣናው ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

"ኢንቨስት በኢትዮጵያ" ፎረም "ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ዝግጁ ናት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች።


 

መንግሥት ተቋማዊ አደረጃጀቱን በመከታተልና ቴክኖሎጂ በማዘመን ለአልሚዎች የተሻለ አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ ዕድገት ልዩ ትኩረት በመስጠት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት በመፈጠሩ የዋጋ ግሽበት ቀንሷል፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችትም አድጓል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደር ስርዓቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መደገፉንና ዘመናዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሳለጠ የመንግስት አገልግሎት እየተሰጠ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስሯን በማሳደግ የቀጣናው መሪ የኢኮኖሚ ማዕከል ሆናለች ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላትና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚፈጠሩባት ሀገር ናት ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የባንክ ስርዓቱም እንዲዘምን መደረጉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአየር መንገድ ግንባታ፣ በቤቶች ልማት እና በሌሎችም ዘርፎች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት በሯ ክፍት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም