የነዳጅ ብክነትን ለመቀነስ ምን ዓይነት ብልኀት መጠቀም ይመከራል? - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ብክነትን ለመቀነስ ምን ዓይነት ብልኀት መጠቀም ይመከራል?
በዮሐንስ ደርበው
ከሰሞኑ የተከሰተውን የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ተከትሎ ነዳጅ ገዝተው የሚጠቀሙ ሀገራት ምርቱን እንደወትሮው እያገኙ አለመሆኑ ይታወቃል፤ ይህም ቀደም ሲል ያስገቡትን በቁጠባ እንዲጠቀሙ እንዳስገደዳቸው ይገለጻል።
ነገሮች ወደነበሩበት እስኪመለሱ ድረስም ሀገራት፤ በአንድ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ ርምጃዎችን እየወስዱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎቻቸውን በመከለስ ዘላቂ መፍትሔ እያማተሩ ነው።
ስለዚህም ህብረተሰቡ ነዳጅን በቁጠባና ብክነትን በሚቀንስ መልኩ እንዲጠቀም ከሚጠቅሙ ተግብራት መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፦
• በሕዝብ ትራንስፖርት የመጠቀም ልምድን ማዳበር ለአብነትም ባቡርን፣
አውቶቡስን እና ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን መጠቀም፤
• ከነዳጅ ይልቅ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን የመጠቀም ልምድን ማስፋት፤
• በነዳጅ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ (Plug-in Hybrid) ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በመተው የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙ ማስቻል፤
• በነዳጅ የሚሠሩትን ወደ ኤሌክትሪክ እና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ሥራን ማጠናከር፤
• በከተማ ውስጥ የሚደረጉ አጫጭር ጉዞዎችን በእግርና በብስክሌት የማድረግ ባህልን ማሳደግ፤
• በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን የሞተር ዘይት፣ ፊልተር እና የጎማ ዓየር ግፊት በየጊዜው ከመፈተሽ አለመቦዘን፤ ወቅታዊ የመኪና ጥገናን ማጠናከርና ኦሪጅናል መለዋወጫዎችን መጠቀም፤
• መኪና አቁሞ መጠበቅ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሲኖር ሞተሩን ማጥፋት፤
• የሞተሩን ጫና ለመቀነስ ጭነት አለማብዛት፤
• እስከ 20 ቶን የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ፤ ከ20 ቶን በላይ የሆኑት ደግሞ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ ማድረግ፤
በሌላ በኩል የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር፤ በነዳጅ ሥርጭትና ግብይት ሂደት ላይ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር በክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች የተጀመረው የተቀናጀ ዘመቻ መጠነ ሰፊ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጿል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመካከላኛው ምሥራቅ በተፈጠረው ቀውስ የተነሣ ነዳጅ ገዝተው የሚጠቀሙ ሀገሮች እንደልብ ለማግኘት መቸገራቸውን አውስተው፤ ችግሩ ተፈትቶ ወደ መደበኛው የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት እስከምንመለስ ድረስ የነዳጅ አከፋፋዮች፣ ማደያዎች እና ተጠቃሚዎች ነዳጅን በቁጠባ፣ ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት በኃላፊነት ስሜት እንዲጠቀሙ ማሳሰባቸው ይታወሳል።