የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
"ኢንቨስት በኢትዮጵያ" ፎረም ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ዝግጁ ናት በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ነው።
ፎረሙ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ፣ አስተማማኝ እና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት፣ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም የወጪ ንግድን የሚያሳድጉ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የኢኮኖሚ ሽግግርን ለሚያፋጥኑ የኢንቨስትመንቶች ዘርፎችን በማመቻቸት አሳይታለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በሁሉም አጋሮች ዘንድ የሚደገፍና በቅንጅት የሚሰራ ነው።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግና እንደ ፋይናንስና የቴሌኮም ዘርፎችን ለግሉ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ፣ የኢንተርፕራይዞችን ሚና የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረው፤ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበረና የዜጎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ሰፊ አምራች ወጣት፣ በመልክዓ ምድር ምቹ የገበያ አማራጮች፣ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ያላት መሆኗን ተናግረዋል።
ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎችም ዘርፎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀይል ፍላጎትን በማሟላት የኢንዱስትሪ አብዮትን ያሳድጋል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በኢትዮጵያና በኢንቨስተሮች መካከል ጠንካራ መተማመንና ትብብርን መፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በአልሚዎች መካከል ውድድርና ትብብር መፍጠር የሚያስችል ሥርዓት ዘርግታለች ብለዋል።
መንግሥት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ለውጦችን ማድረጉን በማንሳት፣ ሪፎርሙ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ ሲባል ከንግግር ባለፈ የተግባር እርምጃ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ አልሚዎች ቁርጠኝነታቸውን በማድነቅ አስፈላጊውን ደጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።