ወርቃማ የቪዛ አገልግሎት የኢንቨስትመንት ዋስትናን የሚያጎናፅፍ ወሳኝ የአሰራር ሥርዓት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወርቃማ የቪዛ አገልግሎት የኢንቨስትመንት ዋስትናን የሚያጎናፅፍ ወሳኝ የአሰራር ሥርዓት ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018(ኢዜአ)፦ ለአስር ዓመታት የሚቆየው የኢትዮጵያ ወርቃማ የቪዛ አገልግሎት ለዓለም አቀፍ አልሚዎች የኢንቨስትመንት ዋስትናን የሚያጎናፅፍ ወሳኝ የአሰራር ሥርዓት መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ።
የቤት ለቤት የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለመስጠትም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ጎሳ ደምሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በቅድመ ሪፎርም ወቅት የፓስፖርት አገልግሎት 270 ሺህ ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የፓስፖርት፣ ጉዞና የይለፍ ሰነድ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን የሚያሳልጥ ስኬታማ የሪፎርም እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት እስከ 4 ሚሊየን የሚደርስ የፖስርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም በመገንባት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በክልል ቅርንጫፎችና ተያያዥ አማራጮችን በማስፋትም የዲጂታል ሥርዓቱን የመፈጸም አቅም ማጎልበት መቻሉን አንስተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተጣለው መሰረትም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በማጠናከር ከተቋማት ጋር የሚናበብ አስቻይ የአሰራር ምኅዳር ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቪዛ አገልግሎቶችም ምልልስን በማስቀረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ እንደተፈጠረ አስረድተዋል።
በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ሀገራዊ ትልም ጋር በማናበብ በኤሌክትሮኒክ፣ የኤምባሲና መዳረሻ የቪዛ አገልግሎትና መሰል ተግባራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፓስፖርት አገልግሎቱን ከነበረበት ኋላቀር የአሰራር በማላቀቅ 8ኛው ትውልድ የኤልክትሮኒክ ፓስፖርት ስራ ላይ ማዋል እንደተቻለ አንስተዋል።
በዚህም በነባርና አዳዲስ ቅርንጫፎች በመደበኛ የፖስፖርት አገልግሎት በ60 ቀን፣ በአስቸኳይ በሁለትና በአምስት ቀናት፤ በፕሪሚየም አገልግሎት ደግሞ በ6 ሰዓታት ውስጥ እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀጣይም የቤት ለቤት የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ደንብ ቁጥር 587/2018 ዓ.ም የአገልግሎት ክፍያ መሠረት ለአስር ዓመት የሚቆይ የወርቃማ ቪዛ (Golden Viza) መካተቱን አስረድተዋል።
የቪዛ አገልግሎቱ አቅም ያላቸው ዓለም አቀፍ አልሚዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ለአስር ዓመታት ያህል በነፃነት መኖር የሚያስቻላቸውን የኢንቨስትመንት ዋስትና እንደሚያጎናጽፍ ገልጸዋል።
በርካታ ሀገራት የጎልደን ቪዛ አገልግሎት እንዳላቸው ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ወርቃማ ቪዛም የሀገርን መገለጫዎችና የደኅንነት ጥራት በማስጠበቅ ኢንቨስትመንትን ለማስፋት አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር አንስተዋል።
በመሆኑም የቪዛ አገልግሎቱን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ የሕንድ ባለሃብት ጋጀንድራ ሲንገህ ማንፑራ፤ የኢትዮጵያ የኢምግሬሽን አገልግሎት የዲጂታል ዘርፍ ሥር-ነቀል ለውጥ የኢንቨስትመንት መታወቂያን ያለአንዳች እንግልት ማሳደስ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ሌላኛው ቻይናዊ ረሚነ ዛነግ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ለአስር ዓመታት በሚቆየው ወርቃማ የቪዛ አገልግሎት የተረጋጋ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራን ለመስራት ወሳኝ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ወጣት መሠረት ጸጋዬ በበኩሏ፤ በኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሰጪ ሙያተኞች ሙያዊ አክብሮት ፓስፖርቷን በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳድሳ ማጠናቀቅ እንደቻለ ገልጿለች።