በምስራቅ ጎጃም ዞን በመስኖ ከለማው መሬት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በመስኖ ከለማው መሬት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል
ደብረ ማርቆስ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን በያዝነው በጋ በአንደኛው ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ላይ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ወዲህ በምግብ ራስን ለመቻል የመስኖ ልማት አንዱ አማራጭ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱም በአንደኛው ዙር ከ41 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ሰብል በመሸፈን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አውስተዋል።
ከ125 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከለማው 41 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የተጠቀሰውን ያህል ምርት መሰብሰብ የተቻለውም ቀድመው ከደረሱ ገብስና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች መሆኑን ጠቁመው ቀሪውን ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም ከ84 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ከ9 ሺህ 700 በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ የአዋበል ወረዳ የሰንበት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጌታሁን ይርሴ እንደገለጹት በመስኖ ልማት በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በመስኖ ካለሙት መሬት 10 ኩንታል ስንዴና 20 ኩንታል የጓሮ አትክልት ማግኘታቸውን አውስተው ዘንድሮ ከዚህ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በዚሁ ወረዳ የወጀል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይከበር ነጋ በበኩላቸው በያዝነው በጋ ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በመስኖ ልማት መሸፈናቸውን አስረድተዋል።
በየዓመቱ ከመስኖ ልማት የሚገኘውን ምርት በመሸጥ ከ60 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ አውስተው ዘንድሮም ከዚህ የበለጠ ገቢ እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።