የምርጫ ካርድ በመውሰድ በድምፃችን የሚመራንን ፓርቲ ለመወሰን ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ካርድ በመውሰድ በድምፃችን የሚመራንን ፓርቲ ለመወሰን ተዘጋጅተናል
ደብረ ማርቆስ ፤መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ) ፡-የምርጫ ካርድ በመውሰድ በድምፃቸው የሚመራቸውን ፓርቲ ለመወሰን መዘጋጀታቸውን የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የበኩላቸውን ለመወጣት የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ቀን ተወስኖ፣ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ስም እንዲሁም የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል ለመወሰን የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት አካሒዷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው አጠቃላይ ምርጫውን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተዘዋውሮ የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ያሉ ዜጎችን አነጋግሯል።
ከየምርጫ ጣቢያዎቹ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎችም የምርጫ ካርድ በመውሰድ በድምፃቸው የሚመራቸውን ፓርቲ ለመወሰን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በከተማው ቀበሌ 11 የሚኖሩትና የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ውባለም ዝይን፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የመምረጥ እድል ያገኙ መሆኑን ተናግረው ካርድ በመውሰድ ለምርጫው ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄዱ የፓርቲዎችን የክርክር መድረኮች እየተከታተሉ መሆኑን አንስተው ለሀገርና ህዝብ ይበጃል ለሚሉት ፓርቲ ድምፃቸውን እንደሚሰጡም ነው የሚናገሩት።
የቀበሌ 10 ነዋሪ የሆኑት አቶ አንተነህ ይርዳው፤ በአምስት አመት አንዴ የሚገኘውን እድል በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመጠቀም የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ጉዳይ የህዝብ የመወሰን መብት የሚረጋገጥበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ከወዲሁ የምርጫ ካርድ በመውሰድ እድሉን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ ከወዲሁ ካርድ በመውሰድ በድምፃቸው የሚመራቸውን ፓርቲ ለመወሰን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትግስት ዳኘ፤ የመራጭነት ካርዳቸውን በመያዝ ድምፃቸውን ለመስጠት ከወዲሁ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደት የዜጎች ተሳትፎ የሚረጋገጥበትና ሀገራዊ ሃላፊነትን የመወጣት ሚና በመሆኑ ለመምረጥ የሁላችንም ዝግጁነት ያስፈልጋል ብለዋል።
የምርጫ ካርድ ከመያዝ በተጓዳኝ ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የበኩላቸውን ለመወጣት የሚሰሩ መሆኑን አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።