አገልግሎቱ 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን የመግጠም ሥራ እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን የመግጠም ሥራ እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን ለነባርና አዲስ ደንበኞቹ የመግጠም ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በፕሮጀክቱ 125 ሺህ ስማርት ሶስት ፌዝ፣ 25 ሺህ ስማርት ነጠላ ፌዝ እንዲሁም 350 ሺህ ኦፍላይን (Semi-Smart) ነጠላ ፌዝ ዘመናዊ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን የመግጠም ሥራ እየተከናወነ ነው።
እስካሁን በተከናወነው ሥራ 60 ሺህ 457 ነጠላ ፌዝ ቆጣሪዎችን እስከ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ዋት ድረስ ኃይል ለሚጠቀሙ ለመኖሪያና ለንግድ ደንበኞች መገጠማቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም 7 ሺህ 13 ባለ ሦስት ፌዝ ቆጣሪዎች ከ8 እስከ 24 ኪሎ ዋት ድረስ ኃይል ለሚጠቀሙ ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተገጥመው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ዘመናዊ ቆጣሪዎች የቅድመ ክፍያ ደንበኞች ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሳይሄዱ የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ቶክን ቁጥር በመግዛት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሞሉ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን ለነባርና አዲስ ደንበኞች የመግጠም ሥራው እየተከናወነ የሚገኘው በ48 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከ67 ሺህ በላይ ደንበኞች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኢትዮ ቴሌኮምና በአዋሽ ባንክ የሞባይል አፕሊኬሽኖች በሳምንት ሰባቱንም ቀናት 24 ሰዓት የትም መሄድ ሳይጠበቅባቸው ቤታቸው ሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት እንዲችሉ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
ይህ ፕሮጀክት ቀደም ሲል የነበሩ የቅድመ ክፍያ ካርድ መጥፋት፣ የካርድ መበላሸት፣ የኔትዎርክ መቆራረጥ እንዲሁም ቆጣሪው ላይ ብር አልገባልኝም የሚሉትን ችግሮች ይቀርፋል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ በሆነ ኃይል መጨመር (Over voltage) ምክንያት የሚመጣን የንብረት አደጋ ይከላከላል፣ ደንበኞች በሚሰጣቸው መሳሪያ አማካኝነት ፍጆታቸውን መከታተል በመቻላቸው አጠቃቀማቸውን መቆጠብ እና ወጪ እንዲቀንሱ ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡