ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ቀሪ ስድስት ሀገራት የሚለዩባቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ቀሪ ስድስት ሀገራት የሚለዩባቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ጣምራ አዘጋጅነት ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
በዓለም ዋንጫው 48 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ እስከ አሁን 42 ሀገራት የተሳትፎ ትኬታቸውን ቆርጠዋል።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ቀሪ ስድስት ሀገራት የሚለዩባቸው የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
የዓለም ዋንጫ የአውሮፓ ጥሎ ማለፍ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ላይ ቱርክዬ ከሮማንያ በቱፕራስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጣልያን ከሰሜን አየርላንድ፣ ዴንማርክ ከሰሜን ሜቄዶኒያ፣ ፖላንድ ከአልባኒያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ከአየርላንድ፣ ዩክሬን ከስዊድን፣ ስሎቫኪያ ከኮሶቮ እና ዌልስ ከቦሲኒያ እና ሄርዞጌቪና በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ45 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፉ ሀገራት ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ወደሚደረገው የመጨረሻ ማጣሪያ ያልፋሉ።
በመጨረሻው ማጣሪያ የጣልያን እና ሰሜን አየርላንድ አሸናፊ ከዌልስ እና ቦሲኒያና ሄርዜጎቪና አሸናፊ፣ የፖላንድ እና አልባኒያ አሸናፊ ከዩክሬንና ስዊድን አሸናፊ፣ የቱርክዬና ሮማኒያ አሸናፊ ከስሎቫኪያና ኮሶቮ አሸናፊ እንዲሁም የዴንማርክ እና ሰሜን ሜቄዶኒያ አሸናፊ ከቼክ ሪፐብሊክ እና አየርላንድ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።
የመጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጨዋታዎችን የሚያሸንፉ አራት ሀገራት ለዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።
አራቱ ሀገራት አስቀድመው በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ 12 የአውሮፓ ሀገራትን ይቀላቀላሉ።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከአውሮፓ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።
በተያያዘም የክፍለ አህጉራት የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታዎችም ይካሄዳሉ።
በማጣሪያው ላይ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (አፍሪካ)፣ ኢራቅ (እስያ)፣ ቦሊቪያ (ደቡብ አሜሪካ)፣ ሱሪናም (ሰሜን/ማዕከላዊ አሜሪካ እና ካሪቢያን)፣ ጃማካይ (ሰሜን/ማዕከላዊ አሜሪካ እና ካሪቢያን) እና ኒው ካሌዶኒያ (ኦሽንያ) ይሳተፋሉ።
በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ያላቸው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (48ኛ) እና ኢራቅ (55ኛ) በቀጥታ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ አልፈዋል።
ቀሪዎቹ አራት ሀገራት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን በሜክሲኮ ያደርጋሉ።
ቦሊቪያ ከሱሪናም ከሌሊቱ 7 ሰዓት በስታዲዩ ቢቢቪኤ፣ ኒው ካሌዶኒያ ከጃማይካ በአክሮን ስታዲየም ከጠዋቱ 12 ላይ ይጫወታሉ።
የኒው ካሌዶኒያ እና ጃማይካ አሸናፊ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የቦሊቪያ እና ሱሪናም አሸናፊ ከኢራቅ ጋር ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያሸነፉ ሁለት ሀገራት ለዓለም ዋንጫው ያልፋሉ።