ቀጥታ፡

የመውረድ ስጋት ያለባቸው ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል። 

ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ይርጋጨፌ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ በአበባ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ይርጋጨፌ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በ13ቱ ተሸንፎ በአምስቱ አቻ ወጥቷል። በ20ዎቹ ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 31 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ 20 ጨዋታዎች አከናውኖ ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናው፤ በ15ቱ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 41 ጎሎችን አስተናግዷል።

አዲስ አበባ ከተማ በተመሳሳይ 11 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 13ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ይርጋጨፌ ቡና ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።  ማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

በአንጻሩ አዲስ አበባ ከተማ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ይወጣል። 


 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ  ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ድሬዳዋ ከተማ እስከ አሁን በሊጉ ማሸነፍ የቻለው ጨዋታ ብዛት ስድስት ነው። 11 ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 18 ግቦችን ሲያስቆጥር 31 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ21 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ 20 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ፤ 14 ጊዜ ተሸንፏል። በአራት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 37 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል። 

ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። አርባምንጭ ከተማ ባለፉት 13 ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ። 

ጨዋታዎቹ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ወሳኝ የሚባሉ ናቸው።


 

ቦሌ ክፍለ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በ31 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ባህር ዳር ከተማ በ16 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ባለፉት አራት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ባህር ዳር ከተማ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም