ቀጥታ፡

የአፍሪካ ወጣቶች አህጉራዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ የራሳቸውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን ይጠበቅባቸዋል - ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ወጣቶች አህጉራዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ የራሳቸውን የወደፊት የተሻለ ዕጣ ፈንታ መወሰን እንደሚጠበቅባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዩዝ ኮኔክት አፍሪካ ኢኒሼቲቭ "ከፖሊሲ ወደ ተግባር ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት በአፍሪካውያን መፍትሄ ማፋጠን" በሚል መሪ ሃሳብ 6ኛውን አህጉራዊ የወጣቶች ዲፕሎማሲ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በኮንፍረንሱ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬን (ዶ/ር) ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የሥራ ኃላፊዎችና የአህጉሪቱ ወጣቶች ተገኝተዋል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት፤ ዩዝ ኮኔክት አፍሪካ ኢኒሼቲቭ የአህጉሪቱን ወጣቶች የእርስ በእርስ ትስስር እያጠናከረ ነው ብለዋል።

በዚህም የአፍሪካ ወጣቶች የዕውቀትና የፈጠራ ክህሎታቸውን በማሳደግ ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግና በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአህጉሪቱን መፃኢ እጣ ፈንታ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገርም ወጣቶች የለውጥ ሞተርነታቸውን የሚያሳልጥ ዕውቀትና ክህሎት መላበስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

6ኛው ዩዝ ኮኔክት አፍሪካ ኢኒሼቲቭ ኮንፍረንስም የአህጉሪቱን ወጣቶች ዕውቀትና ክህሎት በማሻሻል የወጣቶች የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ወጣቶች ጥላ ስር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ወጣቶችም የአህጉራቸውን ብልፅግና ለማረጋገጥና የራሳቸውን እጣ ፈንታ ለመወሰን ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም