በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፡-የአማራ ክልል ሰላምና መረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች፣ከከተሞች እስከ ገጠር ባደረጉት የመስክ ምልከታ የክልሉ ሰላም መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለው ሁኔታ ቀደም ሲል በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚነገረው በተለየ መልኩ እጅግ የተረጋጋ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ያለው ችግር ከፀጥታ ስጋት ይልቅ የአስተሳሰብ ግድፈትና በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱ መረጃዎች የፈጠሩት የስነ-ልቦና ጫና መሆኑን ጠቁመዋል።
ቁጥራቸው በዛ ያሉ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ህይወት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የታጣቂ አመራር አባላት የተከናወኑ የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም ታጣቂዎቹ የልማት ስራዎችን የመደገፍ ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ እጅግ የሚያስደንቁ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተው፤ የክልሉ መንግስትና የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከሩ መምጣታቸውንም አክለዋል።