ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ መሆን የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ መሆን የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ መሆን የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ዜጎች ለኢትዮጵያ ይጠቅማል የሚሉትን ለመምረጥ አስቀድመው የምርጫ ካርዳቸውን እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምርጫ ዝግጅት መልዕክታቸው፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሕዊና ገለልተኛ ሆኖ መጠናቀቁ የህዝብ ተቀባይነት ማስገኘቱን አስታውሰዋል።
ብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የመንግስት ኃላፊነት በመስጠት አስቻይ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተፈጠረው ጤናማ የፖለቲካ ምኅዳርም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት በሀገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ፓርቲው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የሚበጁ አማራጭ ሃሳቦቻቸውን በነጻነት እንዲያቀረቡ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም መከበርን በተመለከተ የማይናወጥ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለዚህም የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተሞክሮዎችን በመቀመር ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በውጤታማነት ማካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የብልፅግና ፓርቲም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባስመዘገባቸው ተጨባጭ ውጤቶች ብቻ በህዝብ ተመራጭ መሆን የሚሻ ፓርቲ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ ፍትሐዊና መልክዓ-ምድራዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም የትውልድና የብሔራዊ ጥቅም አንጓ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የህዝብን አንድነት ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረትም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር የመስራት ባህልን ማጎልበት እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንግስት ለመመስረት የምርጫው ዴሞክራሲዊነት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን በመገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ እያዳረሱ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዜጎችም ድምፅ መስጫ ካርድ መውሰድ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊ፣ ተዓማኒና የህዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።