ለጤናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ለጤናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን አመለከቱ።
በክልሉ በሚዛን አማን ከተማ የአማን ጤና ጣቢያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
በምረቃው ወቅት አቶ ፍቅሬ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት መንግስት የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።
በተለይ በጤና ልማት ሥራው ከመከላከል ባሻገር አክሞ የማዳን ፖሊሲን በመከተል ጤናማና አምራች የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ጠቁመው፤ የጤና ተቋማት ተደራሽነትንና የአገልግሎት ጥራትን ለማስፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ህብረተሰቡ በቅርበት የጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኝ የማስፋፊያ እና የአዳዲስ ጤና ተቋማት ግንባታ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
ከተቋም ግንባታ ባሻገር የሕክምና ግብዓት ማሟላት ሥራ ደረጃ በደረጃ እየተሠራ ሲሆን የመድኃኒት እጥረት እንዳይከሰት በሁሉም መዋቅሮች የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማቋቋም ተግባር መከናወኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለችግሮች መፍትሔ የመስጠት ባህሉን በቅርብ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በማዳበሩ ለዘመናት ጥያቄ ሆነው የቆዩ የአማን ጤና ጣቢያን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀውን የአማን ጤና ጣቢያ ደረጃን ከፍ ለማድረግ በቀጣይ የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎች እንደሚተገበሩ አመልክተዋል።
የጤና ጣቢያው መመረቅ በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የሕክምና ተቋማት ጫና ይቀርፋል ያሉት ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ሌዊ ናቸው።
ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶችን የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የአማን ጤና ጣቢያ መመረቅ በቅርበት የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው የገለጹት ደግሞ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ግራዎ የኪ እና ሀብታሙ ሀይጢ ናቸው።
የጤና ጣቢያ ግንባታን ለረጅም ዓመታት መጠየቃቸውን ገልጸው አሁን ላይ መንግሥት ምላሽ በመስጠቱ መጉላላትን ይቀርፋል ብለዋል።
የአማን ጤና ጣቢያ በከተማዋ ከሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ሦስተኛው ሲሆን በሚዛን አማን እና ዙሪያው ላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
ከጤና ጣቢያው ምረቃ ባሻገር ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነቡ ሦስት ድልድዮችና አንድ የግብይት ማዕከል የመሠረት ድንጋይ በዛሬው ዕለት መቀመጡም ተመልክቷል።