ኢመደአ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢመደአ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
አርባምንጭ፤ መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ከተለያዩ አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በድጋፉም መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሌሎችም በመሳተፍ ለተጎጂዎች አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም በዛሬው ዕለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት በጋሞ ዞን በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አደጋ እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ አደጋው ከተከሰተ ወዲህ ለጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ የሚያገለግል ድሮንና ባለሙያዎችን በመላክ የአየር ላይ ካርታ በማንሳት የበኩሉን ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብና እና ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ መድኃኒቶችን፣ አልባሳትና ምግብ ነክ ቁሳቁስ ለጋሞ ዞን አስተዳደር ማስረከባቸውን ጠቁመዋል፡፡
የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ተግባር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንደሚቀጥልም ዋና ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለተጎጂዎች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ዞኑ ለተፈናቃዮች አስፈላጊ ስፍራ ማዘጋጀቱን ጠቅሰው ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ተግባር እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።