አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ በማድረግ ለወጣቶች ምቹ የልማት ማዕከል የመገንባት ራዕይ በተግባር እየተረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ በማድረግ ለወጣቶች ምቹ የልማት ማዕከል የመገንባት ራዕይ በተግባር እየተረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ በማድረግ ለወጣቶች ምቹ የመዝናኛና የልማት ማዕከል የመገንባት ሥራ በተግባር እየተረጋገጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በአራዳ ፓርክ የወጣቶች የኪነ-ጥበብ እና የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት መርሀ-ግብር አካሂዷል፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በዚሁ ወቅት፤ ከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ማቀድ ብቻ ሳይሆን በተግባር በመፈጸም ውጤታማነቱን እያሳየ ይገኛል።
በወንዝ ዳርቻና በኮሪደር ልማት የተገነቡ የወጣት ማዕከላት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአራዳ ፓርክ የተካሄደው ወጣቶች የተሳተፉበት የባህላዊ ውዝዋዜ፣ የኪነ ጥበብ እና የፈጠራ ስራዎች መርሃ-ግብር ለዚህ ስኬት አብነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ስፍራዎች ወጣቶች አብሮነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩባቸው የጋራ መድረኮች ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉም ብለዋል።
መሰል የማዘውተሪያ ስፍራዎች ወጣቶች በሀገራቸው ላይ ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁና የፈጠራ አቅማቸውን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ምንያህል ጌታቸው እንዳለውም፣ አዲስ አበባ እንደ ስሟ እያበበች መሆኗን ገልጿል።
የተገነቡት ማራኪ የመዝናኛ ስፍራዎች መንግስት ለወጣቱ ትውልድ የሚሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳዩና ተጠቃሚነትን በተጨባጭ ያረጋገጡ ስኬቶች መሆናቸውን ተናግሯል።
ወጣት አርሴማ ሽመልስ በበኩሏ ቀደም ባሉት ጊዜያት በከተማዋ በቂ የወጣቶች መዝናኛ ስፍራዎች እንዳልነበሩ አስታውሳ አሁን የተገነቡት ስፍራዎች ለዓይን ማራኪ ከመሆናቸው ባለፈ፣ ወጣቶች ተሰጧቸውን የሚያሳዩበት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል ብላለች፡፡