ቀጥታ፡

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የመንግስት አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ እያገዘ ነው

ባህር ዳር፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የመንግስት አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመስጠት እያስቻለ መሆኑን የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በብሔራዊ ደረጃ የሚያገኙበት ሕጋዊና መሠረታዊ የመታወቂያ ዓይነት መሆኑም ይታወቃል።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዜጎች በየደረጃው ፈጣንና ፍትኃዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እያስቻለ ነው ።

በተለይም መታወቂያውን ከባንክና ሌሎች አሰራሮች ጋር በማስተሳሰር ወጥ የሆኑ አገልግሎቶችን በፍጥነትና በፍትሃዊነት ለማቅረብ እያገዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በክልሉ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት ከማስቻሉ ባሻገር ህገ- ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የራሱ ድርሻ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመትም ከ4 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መቻሉንም ነው ያመለከቱት።

ፋይዳ የዜጎች ትክክለኛ ማንነት የሚገልፅ መሆኑን አመልክተው ደሕንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም