ቀጥታ፡

ከጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ አገልግሎት አግኝተናል

ጅማ፤መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፡- የጅማ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠቱ ባለፈ ለአቅመ ደካሞችም እፎይታን መስጠቱን  ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ 

ማዕከሉ ስራ ከጀመረ ስድስት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን ነዋሪዎች ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ማዕከል በማግኘታቸው ጊዜና ገንዘባቸውን መቆጠብ ችለዋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የከተማው ተገልጋዮች መካከል አቶ ኑሪ የሱፍ፤ የውኃ እና የመብራት ክፍያዎችን ለመክፈል ከዚህ ቀደም ቀናትን ይወስድባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

እሁን ላይ ግን በከተማው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚፈልጉትን ክፍያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ለነዚህ አገልግሎቶች ሲያወጡ የነበሩትን የትራንስፖርት እና ተጨማሪ ወጪዎች ማስቀረታቸውንም ይገልጻሉ።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙክታር ኢብራሂም ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዘ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ለመሰል አገልግሎት ወደተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በየቀኑ ይመላለሱ እንደነበር ተናግረው አሁን በግማሽ ቀን ውስጥ ተጠናቆልኛል ብለዋል።


 

የጅማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት ከ84 ሺህ በላይ አገልግሎቶችን መስጠቱን የተናገሩት ደግሞ የማዕከሉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ሰለሞን ናቸው።

ወደ ማዕከሉ 25 ሴክተሮች የገቡ ሲሆን በሴክተሮቹ 135 አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን ጠቅሰው 103 ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ምቹ አገልግሎትም እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች ወደ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ቀርበው ከማገልገል በተጨማሪ ልዩ የሊፍት አገልግሎት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በቀጣይ በከተማዋ በሚገኙ ቀበሌዎች ቅርንጫፎችን በመክፈት ይበልጥ ወደ ማኅበረሰቡ ለመቅረብ ታቅዷል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የማዕከሉን አገልግሎት ተንቀሳቃሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አቶ አብዲ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም