ቀጥታ፡

በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

ቦንጋ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚጠፋውን የሰው ሕይወትና የሚወድመውን ንብረት ለመታደግ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ጋር በመተባበር ለአሽከርካሪዎች፣ ለመናሐሪያ የስምሪት ኃላፊዎችና ለአመራሮች የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት ዘርፉ ውጤታማና ጤናማ እንዲሆን የአሽከርካሪዎችንና የዘርፉ ተዋናዮችን አቅም በሥልጠና ማብቃት ወሳኝ ነው። 

እስካሁንም በክልሉ 15 ሺህ አሽከርካሪዎች ሥልጠና መውሰዳቸውንና በትምህርት ቤቶችና በሃይማኖት ተቋማት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘርፉን ለማዘመን 250 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ዘመናዊ የመናሐሪያ ግንባታዎች፣ የተሽከርካሪዎች ብቃት ምዘና ማዕከል እና በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የጥራት ማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በትራፊክ አደጋ የሚጠፋውን የሰው ሕይወትና ንብረት ለመታደግ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ስራ ይጠናከራል ብለዋል። 

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፤ የትራንስፖርት ዘርፉ ለብዙዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የሕዝቦችን እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ መሆኑን አስታውሰዋል።


 

አገልግሎቱን ለማዘመንና ደህንነቱን ለመጠበቅ ኃላፊነት መወጣት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ ሀሰን፤ ባለፉት አራት ዓመታት በዘርፉ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ ካለው ችግር አንጻር አሁንም ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ተናግረዋል። 


 

የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ስልጠና የወሰዱ አሽከርካሪዎች የተሰጣቸውን ሥልጠና ወደ ተግባር በመቀየር እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ መትጋት አለባቸው ብለዋል።

በመድረኩ የክልልና የፌዴራል አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ አሽከርካሪዎችና የመናሐሪያ የስምሪት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም