ቀጥታ፡

በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት አዲስ የንቅናቄ ዘመቻ ተጀመረ

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት አዲስ የንቅናቄ ዘመቻ ተጀመረ።

የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በሐይቁ ህልውና ላይ አደጋ የደቀነውን የእምቦጭ አረም በተደመረ አቅም ለማስወገድ የትብብር ጥሪ አቅርቧል።

ከጣና ሃይቅና አካባቢው የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል የንቅናቄ መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ ሽንብጥ ቀበሌ የጣና ዳርቻ በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ተስፋሁን አለምነህ፤ በጣና ሃይቅ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም በተባበረ ክንድ በማስወገድ የሃይቁን ህልውና መጠበቅ ይገባናል ብለዋል።


 

አረሙን ለማጥፋት በሰው ኃይል እና በማሽን እንዲሁም አጠቃላይ የሕዝቡን ጠንካራ ተሳትፎ ማእከል ያደረገ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የእምቦጭ አረም በቀላሉ የመስፋፋትና የማንሰራራት ባሕሪ ያለው በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ዘመቻ እና የክትትል ስራ የሚያስፈልግ ስለመሆኑም አፅኖት ሰጥተዋል።

በመሆኑም በሐይቁ ህልውና ላይ አደጋ የደቀነውን የእምቦጭ አረም በተደመረ አቅም ለማስወገድ እንዘጋጅ በማለት ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከል ሥራው በሰው ኃይልና በማሽነሪ በመታገዝ እንዲሁም ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በባዮሎጂካል ዘዴ  እየተከናወነ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም