የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከረፋዱ አራት ሠዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቻል በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በ17ቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 58 ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ንግድ ባንክ በ53 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው መቻል በሊጉ እስከ አሁን 20 ጨዋታዎች አከናውኖ 13 ጊዜ ሲያሸንፍ፤ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 37 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 11 ግቦች ተቆጥረውበታል።
መቻል በ44 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ መሪነቱን ያጠናክራል። መቻል ካሸነፈ በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
በ20ኛ ሳምንት ከቦሌ ክፍለ ከተማ በተደረገው ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣችው የመቻል አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ በዛሬው ጨዋታ አትሰለፍም።
ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቡድኖቹ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ20 የሊጉ ጨዋታዎች በ16ቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በ20ዎቹ ጨዋታዎች ላይ 44 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 11 ግቦች ተቆጥረውበታል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ51 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ 20 ጨዋታዎች አድርጎ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ፤ በተመሳሳይ በስምንት ጨዋታዎች ሽንፈት አጋጥሞታል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 20 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 25 ጎሎችን አስተናግዷል።
ሲዳማ ቡና በ28 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሶስት ነጥብ ማግኘት ለቡድኑ የዋንጫ ፉክክር ወሳኝ ነው።
በ20ኛ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ሲዳማ ቡና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
የዛሬ ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ የሚባሉ ናቸው።