ቀጥታ፡

ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይሆን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የታሪክና የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይሆን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የታሪክና የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሳይና ሳቢያ የገጠር ቀበሌ የተገነቡ የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶችን መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል ብለዋል።


 

ይህ ፕሮጀክት ከተማዋን ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም እኩል የማዘመን፣ የማስዋብና በልማት የማሸጋገር ሀገራዊ ራዕያችን በተግባር የታየበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአንድ ወር የግንባታ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ይህ ሞዴል መንደር በአካባቢው ለረጅም ዓመታት የቆየውን የጤና ጣቢያ፣ የመብራትና የውኃ አገልግሎት ጥያቄ በተግባር መልሷል ነው ያሉት።

የአካባቢውን ቁሳቁስ ከዘመናዊ መሃንዲስ ዕውቀት በማሰናሰል በአካባቢው በሚታወቀው የ"ደቢያት" የትብብር ባህል ደግሞ አርሶ አደሩን ቀጥታ በማሳተፍ እጅግ ዘመናዊ ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።


 

የሰዎች መኖሪያን ከእንስሳት መጠለያ በመለየት ለጤናማና ለሥልጡን አኗኗር መሠረት ጥለናል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

ዙሪያውን በተቀናጀ የሌማት ትሩፋት የታጀበው ይህ የገጠር ኮሪደር፣ አርሶ አደሩን የዘመናዊነትና የምርታማነት ባለቤት የሚያደርግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዛሬ ጎንደርም ሆነች ድፍን ሀገራችን ከተማው ብቻ ሳይሆን ገጠሩም እኩል እየተዋበ፣ በልማት እየተገነባና በዕድገት ፍኖት ላይ በጽኑ መሠረት እየተራመደ ይገኛል ብለዋል።

ይህ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የማሸጋገር ትልቁ ማሳያችን ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም