ቀጥታ፡

መሐመድ ሳላህ ሊቨርፑልን በዓመቱ መጨረሻ ይለቃል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፦
የሊቨርፑሉ ኮከብ መሐመድ ሳላህ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ክለቡን እንደሚለቅ በይፋ አስታወቀ።

ሳላህ ይህን ውሳኔውን ያሳወቀው ለደጋፊዎቹ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክት ነው።

 

"ይህ ቀን በመምጣቱ አዝናለሁ... በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ሊቨርፑልን እለቃለሁ። ይህ ክለብ፣ ይህች ከተማ እና ደጋፊዎቹ በህይወቴ ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳላችሁ መግለጽ ይከብደኛል" ብሏል።

የሊቨርፑል ክለብ ባወጣው መግለጫ ሳላህ የዘጠኝ ዓመት የክለብ ቆይታውን በሰኔ 2026 (እ.ኤ.አ) እንደሚያበቃ አስታውቋል።

 

ተጫዋቹ ለደጋፊዎቹ ግልጽነት ለመፍጠር ሲል ውሳኔውን አሁን ለማሳወቅ መምረጡን ቢቢሲ ዘግቧል።

ባለፉት ወራት በሳላህ እና በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት መካከል የነበረው ግንኙነት መሻከር እና የተጫዋቹ የመሰለፍ ዕድል መቀነስ ለዚህ ውሳኔ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ክለቡ እና ተጫዋቹ በጋራ ስምምነት ለመለያየት ወስነዋል።

ሳላህ ምንም እንኳን የቀጣይ ክለቡ በይፋ ባይታወቅም፤ የሳዑዲ ዓረቢያ ክለቦች (በተለይም አል-ኢትሀድ) ተጫዋቹን ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውና ድርድር ላይ እንደሆኑ በስፋት እየተዘገበ ይገኛል።

 

የ33 ዓመቱ ሳላህ በሊቨርፑል 435 ጨዋታዎችን አድርጎ 255 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ይህም ከኢያን ራሽ (346 ጎሎች) እና ከሮጀር ሀንት (285 ጎሎች) በመቀጠል በሊቨርፑል የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ በሶስተኝነት ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም