ቀጥታ፡

በዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ዙሪያ የህዝቡና አመራሩ ትብብርና አብሮነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

ወልዲያ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ በዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ዙሪያ የህዝቡና አመራሩ ትብብርና አብሮነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በሰሜን ወሎ ዞን በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በሰላም፣ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም በሁሉም ረገድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ ሰላምን ማጽናት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ዙሪያ የህዝቡና አመራሩ ትብብርና አብሮነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።


 

የዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በማድረግ ረገድ የመንግስትን ዝግጁነት አንስተው የህዝቡና የሚመለከታቸው አካላት ትብብርና እገዛ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ዜጎች የምርጫ ካርድ በመውሰድ ድምፃቸውን በመስጠት የመወሰን መብታቸውን ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር፤ የማኅበረሰቡና የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት፣ ትብብርና አብሮነት በዞኑ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም በዞኑ ህግ በማስከበር ሰላምን የማጽናትና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር የማድረስ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም