ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ውጤታማ የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ስራዎችን አከናውናለች 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት ረገድ ያላትን የጋራ የመልማት እሳቤና እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ውጤታማ የሃይድሮ  ዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።  

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ''ሃይድሮ ዲፕሎማሲና ቀጣናዊ ትብብር ለዘላቂ ውኃና ኢነርጂ ልማትና አስተዳደር'' በሚል መሪ ሃሳብ ቀጣናዊ ጉባኤ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።  


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት ላይ ያላትን የጋራ የመልማት እሳቤና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ቀደም ሲል ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ክፍተቶች ነበሩ።

ይህንን ለማቃለል ባለፉት አራት ዓመታት ደካማ ጎኖችን የመለየትና ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በተለይም በዓባይና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያተኮሩ በርካታ የምርምር ስራዎች ለዓለም እንዲታወቁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በመረጃ ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ስራ በመሰራቱ ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው እውነታውን እንዲረዱ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ውሃ ዋነኛው የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

በጉባኤው ላይ የታደሙት የጎረቤት ሀገራት ሚኒስትሮችም የቀጣናዊ ትብብርን አስፈላጊነት በአጽንኦት ገልጸዋል። 


 

የደቡብ ሱዳን የውኃና መስኖ ሚኒስትር ጀምስ ማዊች፤ የአየር ንብረት ለውጥና የኢነርጂ ፍላጎት መጨመር በውሃ ሀብት ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሕዊ የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ደቡብ ሱዳን ለዘላቂ ቀጣናዊ ውሃ ሃብት አጠቃቀም ትብብር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።


 

የዑጋንዳ የውሃና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ቢያትሪስ አቲም፤ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ከፉክክር ይልቅ ለትብብር ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

በትብብር ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም