የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲሳኩ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ሚናቸውን የመወጣት ድርብ ሃላፊነት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲሳኩ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ሚናቸውን የመወጣት ድርብ ሃላፊነት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲሳኩ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ሚናቸውን የመወጣት ድርብ ሃላፊነት እንዳለባቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር የፋይናንስ አቅርቦት፣ አካታችነትና ተደራሽነት ላይ ትኩረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እያካሄደ ነው።
ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የዘርፉ ተዋንያን፣ ባለሙያዎች የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት አቅም እንዲጨምር ዓይነተኛ ሚና አላቸው።
የሴቶች፣ የወጣቶችና አርብቶ አደር አካባቢ ያሉ ማህበረሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም ከፍ እንዲል ማድረግ ላይ ቁልፍ ድርሻ እንዳላቸውም አብራርተዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍ ያለ ሚና አላቸው ያሉት ገዥው፤ የድህነት ቅነሳ ተግባራት እንዲሳኩና ብልፅግና እውን እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
ተቋማቱ ለበርካታ ሚሊዮን ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆኑ የዕድገት አጋሮችም ናቸው ያሉት የባንኩ ገዥ ፤ የመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሳለጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ነው ብለዋል።
መንግሥት የፋይናንስ ሥርዓቱን ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር መሰረት የሚጥሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የሞባይል የገንዘብ ዝውውር አማራጮች፣ በዘርፉ ለፈጠራ የተሰጠው ትኩረት የብድርና ቁጠባ ተቋማት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ መልካም ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ተቋማቱ እንደ ሀገር እየተፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የብሄራዊ ባንክም የብድርና ቁጠባ ተቋማት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣትና ሥራ ላይ በማዋል እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
እንደ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጡ በመንግሥት፣ በሕግ አውጪዎች፣ በትምህርት ተቋማትና የልማት አጋሮች መካከል የላቀ ቅንጅት ሊኖር ይገባል።
የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማዊራ ቺቲማ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ጋር በፋይናንስ ተደራሽነት ዙሪያ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በመስኩ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ለማየት ችለናል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የገጠር የፋይናንስ ተደራሽነትም በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉን ተመልክተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ ከበደ በበኩላቸው፤ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረግ ቢችሉም ከሚጠበቀው አኳያ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የፋይናንስ ተቋማቱ ወደ ዘመናዊ አሰራር መሸጋገር እና ተወዳዳሪ መሆን ላይ የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ማህበሩ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
ለአብነትም የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ልምድ በመቀመር በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ብድርና ቁጠባ ተቋማት በማካፈል አቅማቸው እንዲገነባ ማህበሩ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።