የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከግብርና ሽግግር ባለፈ ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከግብርና ሽግግር ባለፈ ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከግብርና ሽግግር ባለፈ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር ከኤች.ፒ.ፒ. ዓለም አቀፍ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንግድ ትርዒት ከዛሬ መጋቢት 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ መንግስት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ምህዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
ለዚህም ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርገው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ እንዲሁም የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የሆርቲካልቸር ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የንግድ ትርዒት አምራቾችን ከዓለም አቀፍ ገዢዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት እንደ ትልቅ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከኬንያ ቀጥላ ሁለተኛዋ አበባ አምራችና ላኪ ሀገር መሆኗን ገልፀው ዘርፉ ለሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ዕድገትና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት፣ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትና የሎጅስቲክስ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀው የዘርፉ ተዋንያን በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋ መኳንንት በበኩላቸው፤ ኤክስፖው ምርትና አገልግሎትን ከማስተዋወቅ ባለፈ በዘርፉ ያሉ ተዋናዮችን በአንድ ጣሪያ ስር በማገናኘት የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የተደገፈና ለዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የኢንዱስትሪ ግንባታ ለማካሄድ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሲሆን፤ ባለፈው በጀት ዓመት 564 ነጥብ 89 ሚሊዮን ዶላር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
ዘርፉ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ደረጄ ደረሮ፤ በአፍሪካ የአቬሽን ዘርፍ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአበባና ፍራፍሬ ምርቶችን ለአለም ገበያ ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አየር መንገዱ በሚሰጠው የጭነት አገልግሎት ወደ አለም የሚላኩትን አበባና ፍራፍሬዎች በፍጥነት ወደ መዳረሻ ቦታዎች የማድረስ ስራ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ክርስቲን ፐረን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ረጅም ዘመን የዘለቀ ታሪካዊ ወዳጀነትና ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአበባ ልማት ኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የሙያ ድጋፍ በማድረግ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቅሰው በቀጣይም ሁሉን አቀፍ ትብብራቸውም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ንግድ ትርዒት ላይ ከ50 በላይ ሀገራት የተወከሉ ሲሆን፤ ከ150 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚ ባለሀብቶች፣ አምራቾች፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና የፋይናንስ ተቋማት እንደሚሳተፉ ታውቋል።
በቆይታውም ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ ዘላቂ ፋይናንስ፣ የምግብ ደህንነት፣ የባህር ጭነት ሎጂስቲክስ እና የአየር ንብረት ለውጥን በሚቋቋሙ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ ያተኮሩ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ውይይቶች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።