ቀጥታ፡

በክልሉ ሰላምን በማጽናት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል

ጋምቤላ ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ሰላምን በማጽናት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሊጠናከሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሠረት ማቲዎስ አሳሰቡ። 

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 5ኛ የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳላፍ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል። ‎ ‎


 

አፈ- ጉበኤዋ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፤ በክልሉ ሰላምን በማጽናት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል።

ባለፉት ወራት በልማትና በመልካም አስተዳደር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም በተወሰኑ ዘርፎች ውስንነቶች እንደነበሩ ከሪፖርቱ መገንዘብ መቻሉን ገልፀዋል። ‎ 

‎በመሆኑም የታዩ ውስንነቶችን በማረምና ጥንካሬዎችን በማስፋት በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ‎ 

‎በቀጣይ ወራት የግብርናና የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ ለስኬታማነታቸው የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል። ‎ ‎

በተለይም ዘንድሮ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሁሉንም የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል። ‎ ‎


 

ምክር ቤቱ በክልሉ የታለሙትን የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲተገበሩ የተለመደውን የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አፈ-ጉባኤዋ ተናግረዋል። ‎ ‎

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ የ2018 ግማሽ በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር፣ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት እቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ በጀት ዓመት የተከለሰ እቅድ ዙሪያ ተወያይቶ አጽድቋል። ‎ ‎

ጉባኤው ስድስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን የአስራ ሁለት የስራ አስፈፃሚዎችን እንዲሁም አራት የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ሹመት መርምሮ በማጽደቅ ማምሻውን ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም