በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ''ምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና'' በሚል መሪ ሀሳብ ለአባል ፓርቲዎች ስልጠና ሰጥቷል።
በዚሁ ወቅት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ፣ በምክር ቤቱ ስር በአባልነት የታቀፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲቀጥል የጋራ ምክር ቤቱ አባላት እስካሁን ሲያደርጉ የቆዩትን ንቁ ተሳትፎ ያጠናክራሉ ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ስልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚገኝ መሆኑን በማመን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።
ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስልጠና የሰጡት በሰላም ግንባታ ዙሪያ የሚሰሩት ለሚ ስሜ፤ ምርጫ በተወሰኑ አካላት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት አለባቸው ብለዋል።
በተለይም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደቱ ፉክክር እና ትብብርን መሰረት ያደረገ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የእስካሁኑ ሂደት የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጥል የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም ስብሰብ ብለው የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ምርጫው ፍትሓዊ እና ነጻ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ህዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መንግስት በተናበበ መልኩ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።