የዲጂታል አሰራርን በማስፋት የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል አሰራርን በማስፋት የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው
ቢሾፍቱ ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል አሰራርን በማስፋት በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የስነ- ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ሁርቃቶ (ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሎችና ፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች 15ኛው ዙር የጋራ የውይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ስነ- ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ሁርቃቶ (ዶ/ር)፤ የሙስና ችግር በሀገር ሁለንተናዊ እድገትና የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ከባድ እንከን ስለመሆኑ አንስተዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የሙስና እና ብልሹ አሰራር መንስኤዎችን በጥናት በመለየት በዘላቂነት የመከላከልና መፍትሄ የማበጀት ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል አሰራርን በማስፋትና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተቋማት እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ስራዎች ዓላማ መካከል አንዱ የሙስና ስጋቶችና ተጋላጭነትን መቀነስ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ ብዙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፉ በእውቀትና ክህሎቱ የዳበረ እንዲሁም በስነ- ምግባር የታነጸ ትውልድ በመገንባት ረገድም እንዲሁ።
በዚህ ጥረት ውስጥ የብዙ ባለደርሻ አካላትና አጠቃላይ የማህበረሰቡ እገዛ፣ ትብብርና የትውልድ ግንባታ ጥረት የላቀ ትርጉም ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ዜጎች በፀረ ሙስና ትግሉ የነቃ ተሳትፎ ያደረጉበትና መልካም ውጤት የተገኘበት መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በቀጣይ ለላቀ ውጤት በጋራ መትጋት ይኖርብናል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው፤ በትውልድ ስነ- ምግባር ግንባታ ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ከመገንባት አኳያ አበረታች ውጤቶች እየተገኘ ነው ብለዋል።
ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በአጠቃላይ ትምህርት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በመንግስታዊ ተቋማት የስነ-ምግባር ግንባታ ላይ የተከናወኑት ተግባራት በዘርፉ ስኬት እንዲመዘገብ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም ሙስናን በመከላከል ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አንስተው ለውጤታማነቱ አጠቃላይ የዜጎች እገዛ፣ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።