ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያስችል የምክክር መድረክና ዓውደ ጥናት አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁርያ አሊ እንደገለጹት፤ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበርና እኩል ተሳትፎአቸውን ለማረጋገጥ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል። 

በተለይም በምርጫ ሂደት የምርጫ ጣቢያዎችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ፣ የምርጫ ቁሳቁሶችና መረጃዎች ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በእጩነትና በውሳኔ ሰጭነት እንዲሳተፉ የማስቻል ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የሲቪክ ማህበራት አካል ጉዳተኞች በምርጫው የነቃ ተሳታፊ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎችም ተግባራት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የክትትልና ድጋፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀይለስላሴ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ በምርጫ ቦርድ እውቅና የተሰጣቸው ከ200 በላይ የሲቪክ ማህበራት የማህበረሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

ለእነዚህ ድርጅቶችም አስፈላጊው የክትትልና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሞክሮዎችን ለሰባተኛው ምርጫ ስኬታማነት ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል። 


 

ለአብነትም በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ የአካል ጉዳተኞች አደረጃጀት መካተቱን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሰው በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የናሸናል ዲሞክራቲክ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ  ፍራንክሊን ኦዱሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያካተተ ምርጫ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

ጉዳተኞች በእጩነት፣ በመራጭነትና በታዛቢነት እንዲሳተፉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም