የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በስኬት ለማካሄድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዘንድሮው ፈተና አስፈላጊ የሆኑ የዝግጅት ስራዎች ቀደም ብለው መጀመሩን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የፈተና ዝግጅት ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።
ባለፈው አንድ ወር ሲካሄድ የቆየው የተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ ዛሬ መጋቢት 15 ቀን 2018 ምሽቱ 11፡30 እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው የምዝገባ ሂደትም ከ500 ሺህ 210 በላይ መደበኛ ተማሪዎች ለፈተናው መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ በድጋሚ ፈተናውን ለመውሰድ በበይነ-መረብ 38 ሺህ 905 ተፈታኞች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሌሎች ወደ 7 ሺህ የሚጠጉ ተፈታኞች ደግሞ በምዝገባ ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ምዝገባው ዛሬ የሚጠናቀቅ በመሆኑ፣ ያልተመዘገቡ ተማሪዎች የተሰጠውን ጊዜ ተጠቅመው እንዲመዘገቡ አሳስበዋል።
የዘንድሮውን ፈተና በበይነ-መረብ ለመስጠት የሚያስችሉ የግብአትና የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎች ከፈተናው በፊት በቂ ልምምድ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር አገልግሎቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ፈተናው ፍጹም ከኩረጃ የጸዳና ተዓማኒነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል፡፡
ከምዝገባ መጠናቀቅ በኋላ ከሚከናወኑ ተግባራትን መካከልም ለተፈታኞች የፈተና ጣቢያዎችን ማሳወቅ፣ የአድሚሽን ካርድ እና የመለያ ቁጥር (ID) ማሰራጨት እና ተማሪዎች በመለያ ቁጥራቸው አማካኝነት በበይነ-መረብ የሙከራ ፈተና እንዲለማመዱ የማድረግ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ፈታኞችን እና የፈተና ሂደቱን የሚመሩ ባለሙያዎችን መመልመልና ስልጠና የመስጠት ሥራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎች ያላቸውን ጊዜ አጋዥ መጽሐፍትንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ለፈተናው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡