ቀጥታ፡

ሴቶች በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል

ሰመራ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ ከለውጡ ወዲህ ባሉት አመታት ሴቶች በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ ገለጹ።

በአፋር ክልል ደረጃ የዘንድሮ ዓለም ዓቀፉ የሴቶች ቀን አከባበር የማጠቃለያ መድረክ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የአፋር ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ መይረም መሐመድን ጨምሮ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ በመድረኩ አንደገለጹት ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል።

በተለይም አርብቶ አደር ሴቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሁሉም ዘርፎች ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጫናዎችን በመቀነስ በተለያዩ ዘርፎች ተሳታፊ ከመሆን ባሻገር ውሳኔ ሰጪ እየሆኑ መምጣታቸውንም አመልክተዋል።

የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ፋጡማ መሐመድ ሴቶች የንብረት ባለቤት መሆናቸውንና በየስራ ዘርፉ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።


 

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሴት አርብቶ አደሮች በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ተሳታፊ እየሆኑ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ሴቶች ተጠቃሚ የሆኑባቸው አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል ብለዋል።


 

በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ተሳታፊነታቸው ከመቸውም ጊዜ በላይ እየተረጋገጠ መምጣቱን ገልፀው መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም