ቀጥታ፡

የትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች የቪዛ ቅጣት ምህረት የመንግሥትን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተግባር የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ የቪዛ ጊዜያቸው ላለፈባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች የተደረገው የቅጣት ምህረት የመንግሥትን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተግባር የሚያሳይ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ።

በኢትዮጵያ የኢሚግሬሽን ሕግና ደንብ መሰረት የተፈቀደላቸው የጊዜ ቆይታ በተለያየ ምክንያት ያለፈባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች የቅጣት ምህረት የማሻሻያ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጎሳ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የቪዛ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ግለሰቦች እናትና አባት ወይም ከሁለቱ አንዱ የኢትዮጵያዊ ዜግነት ማረጋገጫ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ደንብ በመተላለፍ ያለምንም ሕጋዊ ቪዛ የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ግለሰቦች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ መርህ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚሰጠው ክብር መሰረት የጊዜ ቆይታቸው ላለፈባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች የቅጣት ምህረት ማሻሻያ አድርጓል ብለዋል፡፡

በዚህም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች በነጻና ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ደግሞ ካለባቸው የቅጣት ገንዘብ በግማሽ ከፍለው ወደ ሕጋዊ የቪዛ አሰራር መግባት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች ያሳለፈው የቪዛ ቅጣት ማሻሻያ ውሳኔ በጊዜ የተገደበ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንም ከዛሬ መጋቢት 15 እስከ ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት 60 ቀናት አስፈላጊ ሰነዶችን በማሟላት አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡

የቆይታ ጊዜ የቅጣት እፎይታው የኢትዮ-አሜሪካን ወዳጅነት ማዕከል ያደረገ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ትውልደ ኢትዮጵውያን የአሜሪካ ዜጎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እክል እንዳይገጥማቸው እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የቆይታ ጊዜ ያለፈባቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜጎች የቆይታቸውን ሕጋዊነት በማረጋገጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ማሳለጥ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም