በሀረሪ ክልል ነዳጅን በህገወጥ መንገድ ሲሸጡ በተገኙ ማደያዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል ነዳጅን በህገወጥ መንገድ ሲሸጡ በተገኙ ማደያዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ) ፦ በሀረሪ ክልል መንግስት ከወሰነው የነዳጅ ታሪፍ በላይ እንዲሁም ከግብይት ሰንሰለት ውጪ ሲሸጡ በተገኙ ሁለት ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ አስታውቋል።
የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሸሪፍ ሙሜ እንደገለፁት እርምጃ የተወሰደባቸው ነዳጅ ማደያዎች መንግሥት ከወሰነው ታሪፍ በላይ በመሸጥ እንዲሁም ከመደበኛው ገበያ ውጭ በስውር ለጥቁር ገበያ ሲሸጡ በመገኘታቸው ነው።
ነዳጅ ማደያዎቹ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ የፅሁፍና የቃል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንዳልቻሉም ኃላፊው አስረድተዋል።
በዚህም ማደያዎቹ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ምንም አይነት የነዳጅ ምርት እንዳይሸጡ ተደርገዋል ብለዋል።
በነዳጅ ግብይት ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው ጠቁመዋል ።