ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና በዘላቂነት የማቋቋም ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና በዘላቂነት የማቋቋም ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፍትህ ሚኒስቴር በጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

በስፍራው በመገኘት ድጋፉን ያስረከቡት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ በተፈጠረው አደጋ ለተጎዱት ወገኖች ድጋፍና የማቋቋም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዚህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሁን ላይ የ3 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት አበርከቶውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ለአደጋዎች የቅድመ ጥንቃቄ፣ የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት የተቀናጀና የተደራጀ አቅም መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና በዘላቂነት የማቋቋም ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በቀጣይ የአደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱም በተመሳሳይ ለተጎጂዎች የ3 ሚሊየን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፍትህ ሚኒስቴር ለአደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።


 

የክልሉ መንግስት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገልጸው የአደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ ጉዳት እንዳይከሰት በተቀናጀ መልኩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር) እንዲሁ ተቋማቱ ላደረጉት ሰብአዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም