ቀጥታ፡

የሹዋል ኢድ በዓል በደመቀና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል

ሐረር፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ የሹዋል ኢድ በዓልን በደመቀና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐረር ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

በዓሉ ኢድ አል ፈጥር በተከበረ ከስድስተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚያጎለብት መልኩ በተለያዩ ሁነቶች በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።


 

የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር ስነ-ስርዓት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።

በዓሉን በአብሮነት፣ በደመቀና እንግዶችን በማስተናገድ ለማክበር ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው ወጣቶቹ የተናገሩት።

ወጣት ረመዳን ዩስፍ እንደሚናገረው የሹዋል ኢድ በዓልን ለመታደም የተለያዩ እንግዶች ወደ ሐረር እንደሚመጡና እንግዶቹንም ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

በተለይም በዓሉ የክልሉን ባህል፣ እሴትና የመስህብ ሥፍራዎች በስፋት የሚያስተዋውቅ በመሆኑ እንግዶቻችንን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ነው ያለው።

ወጣት ኢዱ አብዱላዚዝ በበኩሉ ዘንድሮ ሐረር ውብና ማራኪ ሆናለች እንግዶችም በሐረሪ ክልል በድምቀት በሚከበረው የሹዋል ኢድ ክብረ በዓል ላይ በአብሮነት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሸዋል ኢድ ወጣቶች በድምቀት የሚያከብሩት፣ ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበትና በጉጉት የሚጠበቅ በዓል መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ፌኔቲ ዱርሳ ናት።

በክብረ በዓሉ ለሚታደሙ እንግዶችም የጎዳና ላይ ትርዒቶችን ጨምሮ ጥንታዊ የሐረሪ ማህበረሰብ ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን ለማሳየት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግራለች።

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ የባህል ዳይሬክተር እስክንድር አብዱረሃማን፤ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሸዋል ኢድ በዓል ላይ በየዓመቱ የሚታደሙ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የሸዋል ኢድ በዓል እንደ ቀድሞ ሁሉ ዘንድሮም አብሮነትን፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ በተለያዩ ሁነቶች በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም