ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ዘገባዎችን መስራት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ መገናኛ ብዙሃን በሀገር ግንባታ ሂደት የማይተካ ሚና አላቸው።

መገናኛ ብዙሃን ሀገር የመገንባት አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ የሚዲያ አጠቃቀማችን የሰከነና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ተቋማቱ በኃላፊነት ካልተመሩ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለሙያዎችና ተቋማት ህዝባዊ አንድነትና ተስስርን፣ ወንድማማችነትንና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ይዘቶች ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህልውና እና ብሔራዊ ጥቅም ቀዳሚ አጀንዳቸው ሊሆን እንደሚገባ በመግለጽ፤ ዘገባዎች በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ዘገባዎችን በዕውቀትና በኃላፊነት መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ቁጥር መጨመሩንና ምቹ የሥራ ምህዳር መፈጠሩን የገለጹት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ለመገናኛ ብዙሃን ዕድገት የተከፈተውን ዕድል ሙያዊ ሥነ ምግባር የተላበሰ ዘገባ በመስራት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡


 

የአሐዱ ሬድዮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ለሀገር ብልጽግና፣ ለማህበረሰብ ልማትና ለሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ሆነው ሊሰለፉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከሀገር በላይ ምንም ነገር የለም ያሉት ጋዜጠኛ ጥበቡ፤ መገናኛ ብዙሃን በኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሚመጥናት ከፍታና ልማት ላይ ለማድረስ መገናኛ ብዙሃን ሂደቱን በማሳላጥ ሚናቸውን መወጣት አለባቸውም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም