ቀጥታ፡

በክልሉ ከ458 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል-ቢሮው

‎ባህርዳር ፤መጋቢት 15 /2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት በአርሶ አደሩ ተሳትፎ በ458 ሺህ 794 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።

‎የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ በዘንድሮ ‎የበጋ ወራት ከዘጠኝ ሺህ የሚበልጡ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ተካሂዷል።

በዚህም ከ458 ሺህ 794 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን ስራዎችን መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

‎እንዲሁም ‎ከ91 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆቱና የተጎዱ ተራራማ ቦታዎችን በመከለል ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተጠብቀው መልሰው እንዲያገግሙ መደረጉንም አመልክተዋል ።

በተጨማሪም ‎ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚበልጡ የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች መከናወናቸውን ጠቁመው የውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦዮች ግንባታ ስራዎችም መካሄዳቸውን ተናግረዋል ።

አርሶ አደሩ  የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በየጊዜው እየተረዳ በመምጣቱ ከዕቅድ በላይ ስራውን መፈፀም እንደተቻለም አስታውቀዋል።

‎በመጭው የክረምት ወቅት ‎በበጋ ወራት የተከናወነውን የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ለማጠናከር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

‎በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዓለሙ ይግዛው እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ መስራት ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ መሬቶች ደን መልበስ ጀምረዋል ።                                                                                                                                                  ‎የእርሻ መሬቶችም የአፈር ለምነታቸው እንዲጨምርና የሰብል ምርታማነት እየተሻሻለ እንዲመጣ ማስቻሉንም ገልፀዋል። 

‎‎የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በየዓመቱ እየሰራን እንገኛለን ያሉት ደግሞ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉነህ ይግዛው ናቸው።

‎ባለፉት ዓመታት በሰራነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተፋሰሶች በማገገማቸው ለእንስሳት ዋነኛ የመኖ  ምንጭ ሆነዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም