ደንቡ የተቋማቱን የመንግስት በጀት ጥገኝነት መቀነስና የሀብት መሰረታቸውን ማስፋት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ደንቡ የተቋማቱን የመንግስት በጀት ጥገኝነት መቀነስና የሀብት መሰረታቸውን ማስፋት ያስችላል
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 15/2018 (ኢዜአ) ፦የራስገዝ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቅል የበጀት ደንብ ተቋማቱ በመንግስት በጀት ላይ ያላቸውን ጥገኝነት መቀነስና የሀብት መሰረታቸውን ማስፋት የሚያስችል መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ ገለጹ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አመዳደብ መመሪያ፣ የመንግስት የከፍተኛ ተቋማት የራስ ገዝነት ሽግግር መመሪያ፣ የራስገዝ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቅል በጀት ድጋፍ ደንብ አዘጋጅቷል፡፡
ሰነዶቹ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1151/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሙያቸው የሰለጠኑ ብቃትና ችሎታ ያላቸው የትምህርት አመራር አባላትን ወደ ሥራ ማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የራስ ገዝ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቅል የበጀት ደንብ ለትምህርት ስርዓቱ ተገቢ ውሳኔዎችን በቅርበት ለማሳለፍ ያግዛል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ራስ ገዝ ናቸው ማለት ሀብት ከተመደበላቸው በኋላ ለችግሮቻቸው ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችሉበት ውሳኔ በራሳቸው ማሳለፍ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ይኸውም ውሳኔው ወደ ተቋማቱ በመውረዱ ነፃነትና ተጠያቂነትን ያሰፍናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ውስን ሀብትን አብቃቅቶ በመጠቀም ጥራትን እንደሚያስጠብቅ ገልጸዋል፡፡
በደንቡ መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ ከሆኑም በኋላ መንግስት መሰረታዊ የበጀት ሥርዓቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ተቋማቱ በመንግስት በጀት ላይ ያላቸውን ጥገኝነት መቀነስና የሀብት መሰረታቸውን ማስፋት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጁት ደንብና መመሪያዎች የአካዳሚ ነፃነትን ለማረጋገጥ ያግዛሉ ብለዋል፡፡
የመማር ማስተማር፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማጎልበት የሚያግዙ ሰነዶች እንደሚሆኑ በመጥቀስ፤ ተቋማት ራሳቸውን የሚፈትሹበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝ አስተዳደርን ለማግኘት አስቀድሞ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ለራስ ገዝነት የሚያበቁ የውስጥ አሰራሮችን፣ የፖሊሲ ዶክመንቶችንና ሌሎች ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ደንብና መመሪያዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግራሉ ብለዋል፡፡
ሰነዶቹ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት እየተደረገባቸው የዳበሩና የተሻሻሉ መሆናቸውን በማንሳት፤ ዘመኑን የዋጁ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አመዳደብ መመሪያ ከዘመኑ ውስብስብ የአስተዳደር ስርዓት ጋር መራመድ የሚያስችል ሰነድ ነው ብለዋል፡፡