ሃዋሳ ከተማ ከሸገር ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ሃዋሳ ከተማ ከሸገር ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከሸገር ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ 20 ጨዋታዎች አድርጎ 12 ጊዜ ድል ሲቀናው በሁለቱ ተሸንፏል። በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 34 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ42 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 20 ጨዋታዎች መካከል 12ቱን ያሸነፈው ሸገር ከተማ በበኩሉ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል።
በ20 ጨዋታዎች 33 ግቦችን ሲያስቆጥር 23 ጎሎችን አስተናግዷል። ሸገር ከተማ በ39 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሃዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። ካሸነፈ ከመቻል የሶስተኝነት ደረጃን በጊዜያዊነት ይረከባል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሸገር ከተማ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ልደታ ክፍለ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ በቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ በ13ቱ ተሸንፎ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 21 ግቦችን ሲያስቆጥር 40 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ15 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ እስከ አሁን በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 20 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ሲያሸንፍ በዘጠኙ ሽንፈት አስተናግዷል። ስድስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
14 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 37 ጎሎች ተቆጥረውበታል። አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
ልደታ ክፍለ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች፣ አዳማ ከተማ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፉም። ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት እስከ መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን በ53 ነጥብ ይመራል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ51 ነጥብ ይከተላል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ22 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በ16 ጎሎች ትከተላለች።